የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነጻ የትምህርት እድል ፕሮጀክት
የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነጻ የትምህርት እድል ፕሮጀክት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ማእከል ሆና ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚያስፈልጋትን የሰው ሀይል በእውቀት መግባ በስነ ምግባር ኮትኩታና አሳድጋ አበርክታለች፡፡ በዚህም ለቤተ ክህነት እና ቤተ መንግሥት ከአገልጋይ ካህናት እስከ ቅዱሳን ነገሥታት ማፍራት ችላለች፡፡ ነገር ግን ይህ አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜ በተነሱ ስሁት ርዕዮተ ዓለማዊ ፈተናዎች እየተዳከመ የመጣ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን ችግሩን ተረድቶ የአብነት ትምህርትና ዘመናዊ (አስኳላ) ትምህርት ተናበው እንዲሔዱ ሁለቱም ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ በሁለት በኩል የተሳሉ አገልጋዮች እንዲፈሩ ለማድረግ በታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ (ዳግማዊ ቄርሎስ) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተሰየመ ነጻ የትምህርት እድል (scholarship) መርሐ ግብር ቀርጾ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ ልዩ ልዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ እና ተጨባጭ ለውጦች ማምጣት ተችሏል፡፡ በዚህ መሠረትም ከዘመናዊ ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚገቡ የነጻ የትምህርት እድሉ ተጠቃሚዎች በተመረጡ ጉባኤ ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚደረግ ሲሆን ከአብነት ወደ ዘመናዊ እንዲሁም በመንፈሳዊ ኮሌጆች እንዲማሩ እድሉ የተሰጣቸው መምህራንና ደቀመዛሙርት በተመደቡበት የትምህርት ተቋም ወጪያቸውን በመሸፍን እንዲማሩ ይደረጋል፡፡
የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት
- በትውልዱ መካከል የተከፈተውን ክፍተት (ከ1960 ዎቹ በኋላ ከቤተመንግስትና ቤተ ክህነት መለያየት በኋላ) ይሞላል ድልድይ ሆኖ ያገናኛል፤
- ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ መሪዎችን ከማፍራት አንጻር አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
- ዓለም አቀፍ አገልግሎት እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ከመፈጸም አንጻር የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
- የአብነት ትምህርትን በትውልዱ ከማስፋፋትና ተወዳጅ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው ሰፊ ነው፡፡
የፕሮጀክቱ ግብ
ሁለንተናዊ አቅምና ዝግጁነት ያላቸው በስነ ምግባር የታነጹ አገልጋዮችንና መሪዎችን ለቤተክርስቲያን ብሎም ለሀገራችን ማፍራት፡፡