በአፋር ሀ/ስብከት የአዋሽ አርባ ቅ/ሚካኤል አብነት ትምህርት ቤት
በአፋር ሀ/ስብከት የአዋሽ አርባ ቅ/ሚካኤል አብነት ትምህርት ቤት
$1,570 of $130,510 raised
የአፋር ሃገረ ስብከት በኢትዮጵያ ጠረፋማና በረሃማ አካባቢ የሚገኝ፣ ለውጪ ኃይሎች ጦርነትና ለሃይማኖት ወረራ በይበልጥ የተጋለጠ በመሆኑ ክርስትና እንደሌሎቹ ከፍተኛ አካባቢዎች (Highland Areas) የተስፋፋበት አይደለም፡፡ በሃገረ ስብከቱ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናትም በብዙ ውጣ ውረድ የተመሠረቱና በአህዛብ የተከበቡ በመሆናቸው ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምዕመኖቻቸው ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ገቢያቸው አነስተኛ ነው፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ አደረጃጀታቸው ደካማ የሚባል ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ያሏቸውን ጥቂት ምዕመናን በአግባቡ የማስተዳደር፣ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ የመፈፀም ደረጃ ላይ የደረሱ አይደሉም፡፡ ይህ ሃገረ ስብከት ቀድሞ በደቡብ ወሎ፣ በምዕራብ ሐረርጌ እና በትግራይ፣ ምስራቅና ሰሜን ሸዋ አህጉረ ስብከት ሲካለሉ የቆዩ ቦታዎችን የያዘ ሲሆን በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ቅዱሳን አበው ተዘዋውረው እንዳስተማሩበት የጽሑፍ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
አካባቢው በአብዛኛው በእስልምና እምነት ተከታዮች የተያዘ በመሆኑ አገልጋይ ካህናቱ በሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች ተምረው ወደዚህ አካባቢ በመፍለስ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ አብያተክርስቲያናት አገልግሎታቸው የሳሳና በየጊዜው አገልግሎት የሚስተጓጎልባቸው ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ቅዳሴ የሚቀደስባቸው በሰንበትና በወርሃዊ በዓላት ብቻ ነው፡፡ ዓመታዊ በዓላት ለማክበር የሌሎች አድባራት ካህናትን እገዛ ይጠብቃሉ፡፡ ዘወትር የሚቀደስበት አንድም ቤተክርስቲያን የለም፣ በዓብይ ጾም እንኳ የሚቀደስባቸው እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ካሉት አብያተክርስቲያናት መካከልም በቁጥር ከአምስት በላይ የሚሆኑት የከፋ የአገልጋይ ካህናት እጥረት ያለባቸውና ለመዘጋት የተቃረቡ ናቸው፤ ይህም አጠቃላይ ሁኔታ በዋናነት ከአገልጋይ ካህናት እጥረት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ከቅዳሴ ልዑካን መሟላት አንጻር ሲታይም በአካባቢው አገልግሎቱ ከሚስተጓጉልባቸው ምክንያቶች በዋናነት የአገልጋይ ካህናት እጥረት ነው፡፡ ብዙዎቹ አብያተክርስቲያናት ቅዳሴ ለመቀደስ የሚያስችላቸው ልዑካን የተሟላላቸው አይደሉም፡፡ ይህም በመሆኑ የቅዳሴ አገልግሎት ለመፈጸም የወር በዓላትን ወይም ዓመታዊ የንግስ በዓላትን መጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ በአካባቢው የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሚፈለገው መልኩ ስላልተስፋፋ የካህናት፣ የዲያቆናት፣ የሊቃውንት፣ የሰባክያነ ወንጌል እና በአጠቃላይ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚመሩ አገልጋዮች እጥረት በአካባቢው ሥር የሰደደ ችግር ነው፡፡ በቅጥር ለመሸፈን የሚደረገው ጥረትም የሚቀጠሩት አገልጋዮች ከአካባቢው ባህልና ሞቃታማው የአየር ሁኔታ ጋር ለመላመድ ስለሚቸገሩ በራሱ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለሆነም ምዕመናኑ ከራሳቸው በሚወጡ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሊቃውንት፣ ሰባክያነ ወንጌል በአጠቃላይ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚመሩ አገልጋዮች ቢገለገሉ የበለጠ የኔነት ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ሥር የሰደደ ችግር አንዱና ዋነኛው መፍትሔ በአካባቢው የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም እነዚህን አገልጋዮች በብዛትና በጥራት ማፍራት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የአፋር ሀገረ ስብከት በገጠርና በከተማ ከ40 በላይ አብያተክርስቲያናት ቢኖሩትም በቂ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሊቃውንት፣ ሰባክያነ ወንጌል በአጠቃላይ የቅድስት ቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚመሩ አገልጋዮች ባለመኖራቸው ምክንያት መንፈሳዊ አገልግሎቱን በበቂ ሁኔታ ማከናወን አልተቻለም፡፡ ከሀ/ስብከቱ በተገኘው መረጃ መሰረት ካሉት አብያተክርስቲያናት መካከል አብዛኛዎቹ አገልጋይ ያልተሟላላቸውና በከፊል አገልግሎት የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ ከአምስት በላይ የሚሆኑት ደግሞ በአገልጋይ እጥረት ምክንያት አገልግሎታቸው እጅግ በጣም የሳሳና ብዙ ጊዜ አገልግሎት የማይሰጥባቸው በመሆኑ ለመዘጋት የተቃረቡ ናቸው፤ ስለዚህ አገልጋዮችን በብዛትና በጥራት ማፍራት ዋነኛ መፍትሔ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አስፈላጊነት በሀገረ ስብከቱ የአብነት ትምህርት ቤት ማቋቋም ያስፈለገው ፡-- የቤተክርስቲያን ተረካቢ የሚሆኑ የአካባቢውን ልጆች በማስተማር አገልጋዮችን በሚፈለገው መጠን ለማፍራት ያስችላል፣
- የአብነት ትምህርት ቤቱ በየሁለት ዓመቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር በሀገረ ስብከቱ በአገልጋይ እጦት ምክንያት የተጓደለውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲጠናከር እና የተዘጉትን እንዲከፈቱ ያደርጋል፣
- ለምዕመናኑ በቂ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት እና በአካባቢው ቋንቋ ወንጌል በማስተማር ያመኑትን በሃይማኖታቸው ፀንተው እንዲቆዩ ለማድረግ፣ የጠፉትን ለመመለስ እና ያላመኑትን ለማሳመን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስለሚኖረው ይህንን ፕሮጀክት መቅረፅ አስፈላጊ ሆኗል።
- በየሁለት ዓመት ግብረ ድቁና ተምረው የሚያጠናቅቁ 30 የአብነት ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚያስችል የአብነት ትምህርት ቤት መገንባት ፣
- በየሶስት ዓመት ቅኔ ተምረው የሚያጠናቅቁ 10 የአብነት ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚያስችል የአብነት ትምህርት ቤት መገንባት ፣
- ከአብነት ትምህርቱ ጎን ለጎን መሰረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት ትምህርት እና የስብከት ዘዴን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ናቸው፡፡
- የጉባኤ ቤት /የመማሪያ ክፍል/ ግንባታ
- የመመገቢያ አዳራሽ ቤት ግንባታ
- እና ዕቃ ማስቀመጫ ቤት ግንባታ
- ቤት እና የገላ መታጠቢያ ቤት እና ልብስ ማጠቢያ ግንባታ
- የተማሪዎች ምልመላ፣ ቅበላ እና ሥልጠና
ተ.ቁ | የወጭ ዝርዝር | መለኪያ | ጠቅላላ ዋጋ |
1 | የግንባታ ወጭ | ብር | 2,640,000.00 |
2 | የውስጥ ቁሳቁስ ወጭ | ብር | 450,000.00 |
3 | የሥልጠና ወጭ | ብር | 87,615.00 |
4 | ጠቅላላ ድምር | ብር | 3,177,615.00 |
5 | ስራ ማስኬጃ (15%) | ብር | 476,642.25 |
3,654,257.25 |